የስማርት ስልኮች ስርጭት እንደ ሌላው የአለም ክፍል ሁሉ በሀገራችን  ኢትዮጵያም  እየጨመረ ይገኛል። የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችም ቁጥር ተያይዞ በማሻቀብ ላይ ነው። ከዚህ ዕድገት ጋር ተያይዞ በአብዛኛው የሞባይል  ኢንተርኔት ተጠቃሚ ዘንድ የሚነሳ ጥያቄ  ፦ “ስልኬ ኢንተርኔት ስጠቀም ብዙ ብር ይበላብኛል” የሚል ነው።

በመሆኑም ኢንተርኔት በመጠቀማችን ከሚያጋጥመን የተጋነነ ወጪ ለመትረፍ የሚያስችሉንን መፍትሄዎች ቀጥለን እናያለን፡፡

1 የባክግራውንድ ዳታን መገደብ (ሪስትሪክት ማድረግ)

በስልካችን ላይ የሚገኙ አፕሊኬሽኖች ከዘጋናቸውም በኋላ በስተጀርባ ይሰራሉ። በተለይም ዳታ የሚፈልጉ እንደ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም እና ሌሎችም አፕሊኬሽኖች ሳንከፍታቸው እንኳን ለማስታወቂያዎች(notifications) እና ለሌላም አገልግሎቶች ኢንተርኔት ይጠቀማሉ። ይህ ደግሞ ሳናስበው ላላስፈላጊ ወጪ ይዳርገናል

ባክግራውንድ ዳታን ለመገደብ በመጀመሪያ በስማርት ስልካችን Setting ውስጥ በመግባት Data Usage የሚለውን ምርጫ ፈልገን Restrict Background Data የሚለውን ምርጫ መምረጥ እንችላለን፡፡ ይህ ሂደት እንደ ስማርት ስልካችን ስሪት ሊለያይ ይችላል።

2 Automatic Update ን መከልከል

በሁሉም የአንድሮይድ ስልኮች ላይ ተጭነው ከሚመጡ አፕሊኬሽኖች መካከል ጉግል ፕሌይ ስቶር አንዱ ነው፡፡ ይህ አፕ በስልካችን ላይ አዳዲስ አፕሊኬሽኖችን ለመጫን ይረዳናል፡፡ ከተጫኑም በኋላ ማሻሻያዎች በሚኖሩበት ሰአት ያወርድልናል፡፡  እነዚህን ማሻሻያዎች(updates) በዳታ ለማውረድ መሞከር ብራችንን ይበላብናል። በአብዛኞቹ ስልኮች ላይ ደግሞ ፕሌይ ስቶር እነዚህን ማሻሻያዎች ያለተጠቃሚው ጥያቄ በራሱ ያወርዳል።

ይህንን አሰራር በቀላሉ ለመቀየር የፕሌይስቶር አፕሊኬሽንን መክፈት፣ በመቀጠልም Setting ውስጥ መግባት፣ ከሚመጡልን ምርጫዎች መካከል Auto-update apps የሚለውን መጫን፣ ቀጥለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ደግሞ Don’t auto-update apps የሚለውን በመምረጥ ስንፈልግ ብቻ ማሻሻያዎችን  ማውረድ ካላስፈላጊም ወጪ መዳን እንችላለን፡፡

3 የዳታ አጠቃቀም ማስጠንቀቂያዎችን መጠቀም

የዳታ አጠቃቀማችን የተለመደ ነው ከምንለው  ውጪ ሲሆን ስልካችን እንዲያስጠነቅቀን አልፎም የሞባይል ዳታ እንዲዘጋ በቀላሉ ማድረግ ይቻላል። ይህ ዘዴ ሳናስበው ከሚያጋጥም የተጋነነ የሞባይል ዳታ ወጪ ይሰውረናል።

ይህን ዘዴ ለመጠቀም በመጀመሪያ በስማርት ስልካችን Setting ውስጥ በመግባት ዳታ ዩዜጅ የሚለውን ምርጫ መምረጥ ይኖርብናል። በመቀጠል Set mobile data የሚለውን ምርጫ በመምረጥ እና በሚታየን ግራፍ ላይ የሚገኘውን ቀይ መስመር ይበቃናል የምንለው የዳታ መጠን ላይ እስኪደርስ ወደ ታች በማውረድ መጨረስ እንችላለን።

4 ለአንዳንድ አፕሊኬሽኖች ዋይፋይን ብቻ መጠቀም

እንደ ዩትዩብ፣ ኢንስታግራም የመሳሰሉ አፕሊኬሽኖች ብዙ ዳታን የሚጠቀሙ እንደመሆናቸው በሞባይል ዳታ ባንከፍታቸው ይመከራል። ስለዚህም እንደነዚህ አይነት አፕሊኬሽኖችን በምንጠቀምበት ጊዜ በዋይፋይ ቢሆን ወጪያችንን በጣም እንቀንሳለን። በተጨማሪም መጠናቸው ከፍ ያሉ ፋይሎችን በዳታ ለማውረድ መቆጠብ ካላስፈላጊ ወጪ ይታደገናል።

5 Battery Saver አብርቶ መጠቀም

Battery Saver በምናበራበት ጊዜ ስልካችን ሃይልን ለመቆጠብ ወሳኝ ያልሆኑ አገልግሎቶችን እና አፕሊኬሽኖችን ይዘጋል በመሆኑም ሳንከፍታቸው ዳታችንን ከሚጠቀሙ አገልግሎቶች በማምለጥ ወጪያችንን መቀነስ እንችላለን ማለት ነው።

ተመጣጣኝ በሆነ ወጪ የሞባይል ዳታን መጠቀም ከምንችልባቸው ዘዴዎች የተወሰኑትን አይተናል። ጠቃሚ መረጃን እንዳገኛቹ ተስፋ በማድረግ በቀጣይም ተመሳሳይ መረጃዎች እንድናቀርብ ሀሳብ እና ጥያቄዎቻችሁን በኮመንት ላይ አድርሱን።

ሰላም!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *